2015 ማርች 24, ማክሰኞ

ስነ ምግባራዊ ሂስ

የስነ ምግባራዊ ሂስ ትንተና
መግቢያ
ስነ ምግባራዊ ሂስ በማህበረሰቡ ዘብድ ያሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ የስነምግባር መርሆኦችን መሰረት በማድረግ በአንድ የስነ ጽሑፍ ስራ ላይ የሚደረግ ምዘና ነዉ። በዚህ ሂስ ሀያሲዉ የቀረበዉ ስነ ጽሁፍ ምን ያህል ስነ ምግባርን ሊያስተምር እንደሚችል ይፈትሻል።  በዚህ አጭር ጽሁፍም ስነ ምግባራዊ ሂስ ምን እንደሚመስል እርቂሁን በላይነህ በ2000 ዓ.ም ያልተጠቡ ጡቶችና ሌሎችም በሚለዉ የአጭር ልቦለድ መድብል ዉስጥ በካራን የተገኘ መሲህ በሚል ርዕስ ያቀረበዉን ልቦለድ በተግባር ለመፈተሽ ሙከራ ይደረጋል።

የልቦለዱ አጽመ ታሪክ
አንድ ማርታ የምትባል ልጅ በካራን ትኖር ነበር። ማርታ አባቷ በህፃንነቷ ስለሞተባት እናትም አባትም ሆና ያሳደገቻት እናቷ ናት። የማርታ እናት ማርታን አሳድጋ አስተምራ  በአንድ መስሪያ ቤት በጸሀፊነት ተቀጥራ እያለች ታመመች። ማርታም ለእናቷ ማሳከሚያ የሚሆን 20 ሺህ ብር ተጠየቀች። ይህን የህክምና ወጭ ከፍላ የእናቷን ህይወት ከሞት ለመታደግ ያላደረገችዉ የለም። እናቷን ለማስታመም ከስራ ስለምጥቀር ከስራዋ ተባረረች፤ ገንዘብ አገኝበታለሁ ብላ ያመነችበትን ተግባር ሁሉ መፈጸም ጀመረች። አስርቱ ትዕዛዛትን ተላለፈች። በሴተኛ አዳሪነት በመሰማራት የእናቷን ህይወት ለማትረፍ ስትል አታመንዝር የሚለዉን ህግ ተላለፈች። በወንዶች ዘንድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ስትል ድንግልና አለኝ በማለት መዋሸት ጀመረች። አይኗን ጭቃ በመቀባትና በመሸፈን ማየት የተሳነኝ በማለት መለመን ጀመረች። ገንዘብ አለዉ ያሰበችዉን ሰዉ ለመዝረፍ ስትል ነፍስ አጠፋች። በመጨረሻም ይህን ሁሉ አድርጋ ሳይሳካላት ቢቀር ፈጣሪዋን በመካድና በፈጣሪዋ ተስፋ በመቁረጥ ወደ ደብተራ (ጠንቋይ) ዘንድ በመሔድ አጋንንት አስጎተተች መጽሐፍ አስገለጠች።

ማርታ ይህን ሁሉ አድርጋ እናቷን ከህመም መፈወስ አልቻለችም። በዚህ ሁኔታ አዝና ተክዛ እንደተቀመጠች ድንገት አማላክ በዐይነ ስጋ ተገልጦ አታቀርቅሪ ይላታል። ማርታ ግን አምላክነቱን አልተቀበለችም። ምክናያቱም አምላኳን ደጋግማ ለምና እናቷ ከህመሟ መፈወስ አልቻለችምና ነዉ። እኔ አምላክ ነኝ ሲላት አይደለህም ትለዋለች፤ ትሰድበዋለች፤ ታንጓጥጠዋለች፤ ትሳለቅበታለች። አምላክ አይደለህም አንተን የሩቁን ጩኸታችንን የማትሰማንን አምላክ ከምናመልክ ይልቅ የቅርቡን የምንዳስሰዉን የምንጨብጠዉን ደንጋዩን ብናመልክ የተሻለ ነዉ በማለት ትጮህበታለች። ከዚያም አምላኳን ትታ ደብተራዉ በነገራት መሰረት እናቷን መድሀኒት ስታጥናት አንድ ጊዜ ድምጽ አሰምታ ፀጥ ትልባታለች። መሲሁንም አንተ ቀናተኛ አምላክ አጋንንት አስጎትቼ መጽሐፍ አስገልጬ አንደበቷን ባስከፍተዉ መልሰህ ዘጋኸዉ በማለት ለፈለፈችበት። መሲሁም አሰርቱ ትዕዛዛቴን አላከበራችሁልኝም፤ በእጄ የፈጠርኳችሁ ፍጡሮቼ አምፃችሁብኛል፤ እያለ ማርታም አምላክ አይደለህም እያለች ስትሳለቅበት ከቆየች በኋላ አምላክ ከሆንክና ስልጣን ካለህ ስልጣንክን በተግባር አሳየኝ ከዚያም አምንሀለሁ አመልክሀለሁ አመሰግንሀለሁ ትለዋለች። ወዲያዉኑ መሲሁ እንግዲያዉስ የልብሽ ይሙላ በማለት ለዓመታት በህመም ስትሰቃይ የኖረችዉን የማርታን እናት ከህመም ፈወሰ፤ ማርታም አምላክነቱን በሚገባ አረጋገጠች፤ ማምስገንም ጀመረች።

በካራን የተገኘዉ መሲህ ከስነ ምግባራዊ ሂስ አንፃር
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በርካታ ሀይማኖታዊ መርሆዎች አሉ። ለምሳሌ አስርቱ ትዕዛዛት ተብለዉ ከሚታወቁት መካከል፦ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ አትግደል፣ ከአምላክህ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ የሚሉት ይገኙበታል። የዕምነቱ ተከታዮችም እነዚህን ሀይማኖታዊ ህግጋት ለመፈፀም ይጥራሉ። በዕርቅ ይሁን በላይነህ በተጸፈዉ ያልተጠቡ ጡቶች በሚለዉ የአጭር ልቦለድ መድብል ዉስጥ ካሉት ልቦለዶች መካከል በካራን የተገኘዉ መሲህ በሚለዉ አጭር ልቦለድ ዉስጥ በርካታ ሀይማኖታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጉዳዮች ተንፀባርቀዋል። የልቦለዱ ዋና ገጸባህሪ ማርታ በልቦለዱ ታሪክ ዉስጥ በተደጋጋሚ የእምነቱ ተከታዮች አጠንክረዉ የሚጠብቋቸዉንና የሚያከብሯቸዉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስትተላለፍ ትስተዋላለች።ሆኖም ግን ደራሲዉ ከስነምግባር አንፃር ማስተላለፍ የፈለገዉ አንባቢዎች ለእናት ያላቸዉ ፍቅር እንዲጨምርና ሀይማኖታቸዉ በሚያዝዘዉ መልኩ ስነምግባራቸዉን ማነጽ እንደሚገባቸዉ ነዉ፡፡
ገጸ ባህሪዋ በርካታ ስነምግባር የጎደለዉ ድርጊት ስትፈጽም ትታያለች። ሆኖም ግን ይህ አይነት ስነ ምግባር የትም ሊያደርስ እንደማይችል በታሪኩ መጨረሻ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። መዋሸት፣ አመንዝራነት፣ መግደል፣ በዛር በጠንቋይ ማምለክ ለዉርደት ለዉድቀት የሚዳርግ እንጂ የትም ሊያደርስ እንደማይችል ተገልጿል። ከታሪኩ ላይ እንደምንረዳዉ ማርታ የእናቷን ህመም በህክምና ለመከታተል ስትል በርካታ ትዕዛዛትን ተላልፋለች። ሆኖም በአንዱም ሲሳካላት አትስተዋልም። ዋሽታም፣ አመንዝራም፣ ነፍስ አጥፍታም ብር ልታገኝ አልቻለችም። የእናቷን ህመምም ማስታገስ አልቻለችም። በመጠኑም ቢሆን ትንሽ የተስፋ ጭላንጭልን ያሳያት የደብተራዉ ሙከራም ለደቂቃ የማይቆይ ተስፋ ሆነባት። ሙከራዋ ሁሉ ባዶ ሆነ። ደራሲዉ ገጸባህሪዋን በዚህ መልኩ ያቀረባትም ሆን ብሎ ይህ አይነት ስነምግባር የትም ሊያደርስ እንደማይችል ለአንባቢያን ለማስወቅ ካለዉ ፍላጎት የተነሳ  ነዉ። የአምላክን ትዕዛዝ ረስቶ ለአዋይ ለጠንቋይ ተገዝቶ እንኳንስ ከህመም መፈወስ አንድ ስንዝር እንኳ መራመድ የማይቻል መሆኑን ታሪኩ ይስገነዝባል። ልቦለዱም ይህ አይነት ስነ ምግባር ማለትም አምላክን የመካድ፣ ትዕዛዛትን ያለመፈፀም ወዘተ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዳይከሰት ለማስገንዘብ ያለዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነዉ።

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በካራን የተገኘ ዉመሲህ ከስነ ምግባራዊ ሂስ አንፃር ሲታይ አንባቢዎችን ጥሩ ስነምግባር ሊያስተምር የሚችል ነዉ። ከማህበረሰቡ ባህላዊ የስነምግባር መርህ አንፃር ሲታይ ዋናዋ ገጸ ባህሪ ለእናቷ የምታደርገዉ በጎ ስራና የምትከፍለዉ መስዋትነት በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉና ሊበረታታ የኒገባዉ ስነምግባር ነዉ። ከሀይማኖት አንፃር ደግሞ ሁሉም ነገር ያለ አምላክ ፈቃድ ሊሆን እንደማይችል ያሳያል። ስለሆነም በአምላክ ማመን እንደሚገባ ያስተምራል።

2015 ማርች 23, ሰኞ

ረጅም ልቦለድ



የረጅም ልቦለድ መከፋፈያ መስፈርቶች
ለረጅም ልቦለድ አይነቶች ወጥ የሆነ የመከፋፈያ መስፈርት አለ ለማለት ቢያስቸግርም አብዛኛዉን ጊዜ ረጅም ልቦለድን ለመከፋፈል ይዘትን ወይም ጭብጥንና በልቦለዱ ዉስጥ የሚቀርቡ ክንዋኔዎችን መሰረት በማድረግ መከፋፈል የተለመደ ተግባር ንዉ። ከዚህም በተጨማሪ የመቀረጹ መቼቶችና ገጸባህሪያት ለልቦለድ መከፋፈያ መስፈርት በመሆን ያገለግላሉ።
ይዘትን ወይም ጭብጥን መሰረት በማድረግ ፖለቲካዊ፣ ስነ ምግባራዊ፣ ስነ ሰባዊ ወዘተ በማለት መከፋፈል ይቻላል። ፖለቲካዊ ርአሰጉዳዮችን የሚያካትተዉን ፖለቲካዊ፣ ስለ ስነምግባር የሚሰብከዉን ስነ ምግባራዊ፣ የማህበረሰቡን ባህላዊና ማህበራዊ እዉነታዎች የሚያንጸባርቀዉን ስነ ሰባዊ ልቦለድ በማለት መፈረጅ ወይም መመደብ ይቻላል።

የሚቀረጹ ገጸባህሪያትን መሰረት በማድረግ ደግሞ አሊጎሪያዊ፣ ታሪካዊ፣ ደብዳቤያዊ ወዘተ በማለት መከፋፈል ይቻላል።የተቀረጹት ገጸባህሪያት እንስሳትና ረቂቅ ነገሮች ወይም ግኡዛን አካላት ከሆኑ አሊጎሪያዊ፣ ታዋቂ ባለታሪኮች ገጸባህሪ ታሪካዊ ቦታወች መቼቶች ሆነዉ የሚቀርቡበትን ደግሞ ታሪካዊ ልቦለድ በማለት መመደብ ይቻላል።

ይሁን እንጂ ከላይ የቀረቡት የመከፋፈያ መስፈርቶች ወጥነት ያላቸዉ ናቸዉ ለማለት አያስደፍርም። ይኸዉም በአንዱ ልቦለድ ዉስጥ የተገለጹ ጉዳዮች በሌላዉ ዉስጥ ሊገኙ የሚችሉ መሆናቸዉ ነዉ። ለምሳሌ በአሊጎሪያዊ ልቦለድ በገጸባህሪያት አማካኝነት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሊተቹ፣ ሊገመገሙና ሊፈተሹ፣ ስነ ምግባር ሊሰበክና አጠቃላይ ስነ ሰባዊ ጉዳዮች ሊገለጹ ይችላሉ። ይህ የአንዱ ልቦለድ ይዘት በሌላዉ ዉስጥ ተካቶ መገኘት የመከፋፈያ መስፈርቱን የተጣራ አለመሆን ያሳያል። ከዚህ በመነሳትም የመከፋፈያ መስፈርቱ ክፍተት ያለበት ነዉ ለማለት ይቻላል። ይሁንና የተለያዩ ትናቶች ተጠንተዉ የተጣራ መክፈያ እስከሚገኝ በዚጅህ መስፈርት መጠቀም ይቻላል።

የረጅም ልቦለድ አይነቶች
የልቦለድ መከፋፈያ መስፈርቶች እነዚህ ናቸዉ ብሎ በርግጠኝነት መናገር እንደሚያስቸግር ሁሉ የልቦለድ አይነቶችንም ይህን ያህል ናችዉ ብሎ ለመወሰን ያዳግታል። በርካታ የረጅም ልቦለድ አይ ነቶች እንዳሉ ብርሐኑ (2009፣ 32) ይገልጻሉ።

ከላይ በቀረበዉ የረጅም ልቦለድ መከፋፈያ መስፈርት መሰረትም የተለያዩ የረጅም ልቦለድ አይነቶች አሉ። እነሱም ፖለቲካዊ፣ ስነ ሰባዊ፣ ስነ ምግባራዊ፣ ደብዳቤያዊ፣ ታሪካዊ፣ አሊጎሪያዊ ምጸታዊ ወዘተ ናቸዉ። ይሁንና የኛ የትኩረት አቅጣጫ ሶስቱን የልቦለድ አይነቶች ማብራራት ወይም መግለጽ በመሆኑ እንደሚከተለዉ ለመግለጽ ተሞክሯል።

ስነ ምግባራዊ ልቦለድ
ይህ የልቦለድ አይነት ከህብረተሰቡ እዉነታ ጋር የተቀራረበ ነዉ። ማለትም በታሪኩ ዉስጥ የሚጠቀሱ ቦታዎችና ስሞች ታሪኩ ከተቀረጸበት ማህበረሰብ ባህል ወግና ልማድ ጋር የተቀራረቡ ናቸዉ። ስነ ሰባዊ ልቦለድ የተቀረጸበትን መቼት (ጊዜና ቦታ) ከማህበረሰቡ ወግና ልማድ ጋር አዋህዶና እዉነታዊ ነትን አላብሶ የማቅረብ አቅም አለዉ። ይህ ልቦለድ ሰወች በእተወሰነ ቦታና ጊዜ የፈጸሟቸዉን፣ ወደፊት የሚፈጽሟቸዉንና እየፈጸሟቸዉ ያሉትን ድርጊቶች ከማህበረሰቡ እዉነታ ጋር በማቀራረብ በገጸባህሪያት አማካኝነት ይገልጻል።
ፖለቲካዊ ልቦለድ
ይህ የልቦለድ አይነት በመተግበር ላይ ያሉ ፖሊሲዎችን፣ የፖለቲካ ሰዎችን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድሪጅቶችን፣የአስተዳደር አካላትን ወዘተ በገጸባህሪያት አማካኝነት በመሳል ስላለዉ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚገልስ የልቦለድ አይነት ነዉ። ይህ የልቦለድ አይነት ያለፈዉ ፖለቲካዊ ስርአት ምን እንደነበር፣ የዛሬዉ ምን እንደሚመስል አዝናኝና እዉናዊ በሆነ መልኩ ይተችበታል።

ፖለቲካዊ ልቦለድ የደራሲዉ የግል ስሜት የሚንጸባረቅበት ሳይሆን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉን ሀሳቦች የሚያቀርብ፣ በቀጥታ ስለ ፖለቲካዊ ክስተቶች የሚገልጽ፣ የሚተረጉምና የሚተነትን ዝርዉ የፈጠራ ስራ ነዉ ሲሉ ሞሪስ ጆሴፍንን ጠቅሰዉ ይገልጻሉ።

በፖለቲካዊ ልቦለድ ዉስጥ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉ ሀሳቦች ወሳኝነት አላቸዉ። መቼቱም አንድ ፖለቲቻ የነበረበት ጊዜና ቦታወች ናቸዉ ሲሉ ኤርቪንግ ይገልጻሉ።

ከእነዚህ ሁለት ምሁራን ሃሳብ የምንረዳዉ ፖለቲካዊ ልቦለድ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸዉን ሃሳቦች የሚገልጽ የደራሲዉ የምናብ ዉጤት መሆኑን ነዉ።

2015 ማርች 14, ቅዳሜ

ድራማ

ድራማ
ድራማ የሚለዉ ቃል የእንግሊዘኛ ቃል ሲሆን ተዉኔት የሚለዉን  የአማርኛ ቃል እንዲወክል ተደርጎ የተሰየመ ቃል ነዉ። ተዉኔት በግጥም ወይም በተዋንያን ድርጊትና ምልልስ ታጅቦ በመድረክ ላይ የሚተወን ድርሰት ነዉ። አንዳንድ ሰዎች ድራማን ትያትር፣ ቤተ ተዉኔት፣ መራሂ ተዉኔት እያሉ ሲጠሩት ይስተዋላል። ነገር ግን እነዚህ ከድራማ ጋር ግንኙነት ያላቸዉ እንጂ ድራማን የሚወክሉ አይደሉም። ለምሳሌ ድራማ የሚቀርብበትን ስፍራ፣ የድራማዉን ድርሰት፣ የድራማዉን ሙያ፣ በመድረክ ላይ ያለዉን የአቀራረብ  ስልት የሚያጠቃልለዉ ቲያትር ሲባል የድራማዉ ደራሲ ወይም ጸሐፊ ደግሞ ጸሐፊ ተዉኔት ይባላል። ጸሐፊ ተዉኔቱ የፃፈዉን ድራማ አዘጋጅቶ ለመድረክ የሚያበቃዉ ደግሞ መራሒ ተዉኔት ይባላል።

ድራማ የተዋንያንን ንግግርና አካላዊ ተሳትፎ አጣምሮ በመድረክ ላይ የሚያቀርብ የሥነ ጽሑፍ  ዘርፍ ነዉ፡፡  የሰዉ ልጅ ስሜት፣ ፍላጎት፣ ፀባይ ገፀባህሪያት በሚወክሉ ተዋንያን አማካኝነት በመድረክ ላይ የሚተወን ጥበብ ሲሆን ይህም ጥበብ በግጥም ወይም በዝርዉ ሊቀርብ ይችላል።

የድራማ ጥንተ አመጣጥ
ድራማ መቼ እና የት ተጀመረ ለሚለዉ ጥያቄ ቁርጥ ያለ መልስ ማግኘት አይቻልም። ምክናያቱም የድራማ ቀለምና አሻራ ያላቸዉ የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች በርካታ ከመሆናቸዉ የተነሳ ነዉ። ነገር ግን መደበኛ መልክ አስይዞ ድራማን ለተደራስያን በማቅረብ ረገድ ግሪኮችን ቀድሞ የተገኘ የለም። በዚች ሀገር ድራማ ከ 2200  ዘመናት በፊት ከጥንታዊዉ የግሪክ ንጉስ  አዳዮናይሲስ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነዉ።

ከግሪኮች በመቀጠል በድራማ ታሪክ ስማቸዉ የሚጠራዉ ሮማዉያን ናቸዉ። ሮማዉያኖች በጥንታዊ የሀይማኖት ክብረ በዓላት በሞእ ጀግና መቃብር ላይ በህብረት የሚዘመሩ መንፈሳዊ መዝሙሮች እና በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ በክዋኔ የሚተረቱ ተረቶች ለድራማ ባህልና ጅማሮ መስፋፋት ምክናያቶች ናቸዉ። ለምሳሌ፦ በግብፅ የንጉስ ፈርኦን መዋለ ንግስና፣ በእንግሊዝ የሼክስፒር ስራዎች ተጠቃሽ ናቸዉ።

የድራማ አነሳስና እድገት በኢትዮጵያ
ለኢትዮጵያ ድራማ አነሳስና እድገት የላቀ አስተዋጽኦና ድርሻ አላቸዉ ብሎ ታሪክ የሚዘክራቸዉ ተክለሀዋርያት ተክለ ምርያም፣ ዮፍታሔ ንጉሴ፣ ከበደ ሚካኤል፣ መንግስቱ ለማ፣ ፀጋየ ገብረ መድህን፣ ተስፋየ ገሰሰና ደበበ ሰይፉ ናቸዉ። እነዚህ ደራሲያን በስራቸዉ ያነሷቸዉ ርዕሰ ጉዳዮችም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ የቀድሞዉንና የዘመኑን የባህል ግጭት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት፣  ግብረገብነት፣ የፍትህ እጦት እና አድሎ ናቸዉ።


ተክለሀዋርያት ተክለማርያም
በአማርኛ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የመጀመሪያዉ ፀሀፊ ተዉኔት ተክለሀዋርያት ተክለማርያም ናቸዉ። እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት ለእትዮጵያ የመጀመሪያ ድራማ የሆነዉን የአዉሬዎች መሳለቂያ ወይም ፋቡላ የተሰኘዉን ተዉኔት ደረሱ። በተዉኔቱም ይዘመኑን የስልጣን ብልግና፣ ኋላቀርነትና ደካማ አስተዳደር ይፋ አውዉጥተዉ አሳይተዋል። ጽሑፈ ተዉኔቱም በግጥም መልክ የቀረበ ነበር።

ዮፍታሔ ንጉሴ
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት የመጀመሪያዉን ድራማ በ1923 ዓ.ም ጥቅም ያለበት ጨዋታ በሚል ርዕስ ደርሰዋል። የድራማዉ ይዘትም ሀይማኖታዊ ነበር። በዚሁ አመት ምስክር የሚል ሌላ ድራማም ደርሰዋል። በ1924 የሆድ አምላኩ ቅጣት እና ያማረ ምላሽ፣ በ1925 ዳዴ ተራ፣ በ1926 ሙሽሪት ሙሽራ፣ የህዝብ ፀፀት፣ ደግን ለመከተልና ክፉን ለመተዉ እንዲሁም ስለ ስጋ ደዌ በሽተኞች አንድ  ዝነኛ ድራማ ደርሰዋል። ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በፊት በ1927 መሼ በከንቱ፣ ጠረፍ ይጠበቅ፣ የደንቆሮዎች ቲያትር የተባሉ ድራማዉችን ደርሰዋል። በኢጣሊያን ወረራ ወቅትም አፍጀሽን የተሰኘዉን ድራማ ደርሰዋል። ይህ ስራቸዉ ድራማ የመፃፍ ችሎታቸዉን ያሳዩበት ድራማ ነበር። ዮፍታሔ በወቅቱ ድራማ ለመፃፍ ያነሳሳቸዉ አስተማሪ ስለነበሩ የድራማን ጥበብ በተግባር ለማሳየትና ድራማ ይመለከቱ ስለነበር እንዴት መቅረብ እንዳለበት ለማሳየት ያላቸዉ ፍላጎት እንደነበር ይነገራል።

በአጠቃላይ ዮፍታሔ ንጉሴ እስከ 1928 ዓ.ም በጠቅላላዉ 16 ድራማዎችን ደርሰዋል። ድራማዎችም በየመድረኩ በተደጋጋሚ ታይተዋል። የዚህ ዘመን ድራማ አባት በመባልም ይታወቃሉ። በ1939 እያዩ ማዘን የተሰኘዉን ባለ 5 ክፍል ድራማ ጽፈዋል። ይህ ድራማም በፀሀፈ ተዉኔቱ መራሔ ተዉኔትነት ተዘጋጅቶ በመድረክ ቀርቧል።

ከበደ ሚካኤል
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት በግጥም ወይም በቅኔ ጥበብ የተቀኙና ወደ ድራማዉ አለምም ያዘነበሉ ነበሩ። በዚህ ረገድም አኒባል፣ ካሌብ፣ የትንቢት ቀጠ (ችሎታቸዉን ያሳዩበት) እና የቅጣት ማዕበል የተሰኙ ድራማዎችን ጽፈዉ ለመድረክ አበርክተዋል። የሼክስፒርን ሮሚዮና ጁሌትን እና የበርታ ክሌንን ከይቅርታ በላይ የተሰኙ ድራማዎች ወደ አማርኛ መልሰዋል።

መንግስቱ ለማ
እኒህ ፀሀፊ ተዉኔት በአዲስ የድራማ አቀራረባቸዉ የሚታወቁ ሲሆኑ ኮሚዲ የተባለዉን የድራማ ዘዉግ ለኢትዮጵያ አስተዋዉቀዋል። በርከት ያሉ ድራማዎችንም ለኢትዮጵያ አበርክተዋል። ከነዚህም መካከል፦ጠልፎ በኪሴ (ኮሚዲ የተዉኔት ዘዉግን ያሳዩበት)፣ ያላቻ ጋብቻ፣ በ1968 ባለካባና ባለዳባ፣ በ1969 ዘኢንስፔክተር የሚለዉን ድራማ ጠያቂዉ በሚል ር ዕስ ተርጉመዋል። በ1974 ፀረ ኮለኒያሊስት፣ በ1978 ሹም ያ እና የአንቶኒቸኮቬ ዘ ብሔር የተሰኘዉን ዳንዴዉ ጨቡዴ፣ የተዉፊክ አል ሀኪምን ላስት ቱ ኪል የተሰኘዉን ግደይ ግደይ አለኝ በሚል ባለ አንድ ገቢር ትይንቶች ተርጉመዋል። በድህረ አብዮትም  ባለ አንድ ገቢር የሆነዉን የዐለሙ ንጉስ የተሰኘዉን ድራማ ፅፈዋል።

ነጋሽ ገብረማር ያም
ይህ ጸሀፊ ተዉኔት በስራዎቹ ፖለሪካን ፊት ለፊት ይጋፈጥ ስለነበር አብዛኛዎቹ ስራዎች ተቃጥለዋል። ከተገኙት ተዉኔቶች መካከል የድል አጥቢያ አርበኛ እና የአዛዉንቶች ክበብ ተጠቃሽ ሲሆኑ ይዘታቸዉን ግን ለማወቅ እንዳልተቻለ ምሁራን ያስረዳሉ።

ፀጋየ ገብረ መድህን
በ1950ዎቹ ከከሸፈዉ መፈንቅለ መንግስት ጋር ተያይዞ የተነሳዉን የለዉጥ ሐሳብና በትዉልዶች መካከል በተከሰቱ የአስተሳሰብ ልዩነቶች የተነሳ ይንፀባረቅ የነበረዉን የባህል ግጭት በድራማወቻቸዉ ያነሱ ነበር። ትራጄዲ የተሰኘዉን አዲስ የድራማ ዘዉግም አበርክተዋል። የፀጋየ የድራማ ስራዎች በከፊል በልግ፣ የከርሞ ሰዉ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ አቡጊባ ቀይሶ፣ መል ዕክተ ወዝ አደር፣ ሰቆቀዎ ጴጥሮስ፣ ሀሁ ወይም ፐፑ፣ እናት ዐለም ጠኑ፣ የራሱ ጽሑፈ ተዉኔቶች ሲሆኑ ከሼክስፒር የተተረጎሙ ስራዎች ደግሞ ኦቴሎ፣ ሀምሌትና ማክቤዝ ናቸዉ። ከፈረንሳዩ ፀሀፊ ተዉኔት ሞሊቬር የተተረጎመዉ ደግሞ ሙዚቀኛዉ ጆሮ ይገኙበታል። ቴዎድሮስ የተሰኘዉን የእንግሊዘኛ ድራማም ወደ አማርኛ ተርጉሟል።

ተስፋየ ገሰሰ
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት በአሜሪካን አገር እያለ በ1953 ዓ.ም በእንግሊዘኛ ላቀችና ማሰሮዋ በሚል ጽፏል። በ1954 የሺን፣ በ1958 አባትና ልጆች፣ በ1961 ዕቃዉ የተሰኙ ድራማዎችን ጽፏል። እቃዉ የሚለዉ ድራማ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመድረክ ለመታየት የበቃ ነዉ። የዚህ ድራማ ርዕሰ ጉዳይም የሰዉ ልጅ ሲጨቆን፣ ሲንገላታና ሲሰቃይ ከዚህም አልፎ እንደ ዕቃ ተቆጥሮ ሰብአዊ ክብሩን ሙሉ በሙሉ ሲያጣ ይታያል። ድራማዉ ይህንን አይነት ድርጊት ያወግዛል።

ደራሲዉ ከነዚህም በተጨማሪ በ1966 ማነዉ ኢትዮጵያዊ፣ በ1970 ፍርዱን ለዕናንተዉ፣ በ1972 ተሀድሶ፣ በ1979 ሰኔና ሰኞ የተሰኙ ድራማዎችን ለመድረክ አብቅተዋል። ተስፋየ ጸሐፊ ተዉኔት ብቻ ሳይሆኑ መራሒ ተዉኔትም ተዋናይም ነበሩ።

ደበበ ሰይፉ
እኒህ ጸሐፊ ተዉኔት ከባህር የወጣ ዓሳ፣ ሳይቋጠር ሲተረተር፣ እነሱ እሷ፣ እናትና ልጆቹ የሚሉ ድራማዎችን ደርሰዋል፤ መራሒ ተዉኔትም ተዋናይም ነበሩ።

ብርሀኑ ዘሪሁን
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት በ1972 መረሸን፣ በ1975 ጣጠኛዉ ተዋናይ፣ በ1972 ባልቻ አባነፍሶን ደርሰዋል።

ስንዱ ገብሩ
እነህ ፀሀፊ ተዉኔት የመጀመሪያዋ ሴት ፀሀፊ ተዉኔት ሲሆኑ በ1938 ኮከብህ ያዉና ያበራል ገና የሚለዉን ተዉኔት የመጀመሪያ ስራቸዉ አድርገዉ አቅርበዋል።  በ1939 የየካቲት ቀኖች (ደራሲዋ የምትታወቅበት)፣ የሚል ድራማ የደረሱ ሲሆን ይዘቱም የየካቲት 12ቱን ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ የሚዘክር ነበር። በ1940 የታደለች ህልም፣ ርዕስ የሌለዉ ትዳር፣ የኑሮ ስህተት፣ በ1943 ከማይጨዉ መልስ፣ ፊታዉራሪ ረታ አዳሙ የተሰኙ ተዉኔቶችን ደርሰዋል። ያበረከቷቸዉን አስተዋፅኦ ስናይ ከነ ዮፍታሔ ንጉሴ፣ አፈወርቅ አዳፍሬ፣ ተስፋየ ለማ ፣ አበበ ረታ፣ ልጅ አርዓያ ስላሴ ጋር በመሆን ማዘጋጃ ትያትር ቤትን መስርተዋል።  

ኢዩኤል ዮሐንስ                                        
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት በረከት ያሉ ጽሑፈ ተዉኔቶችን ደርሷል። ከነዚህም መካከል፦ የህይወት ፋና የወጣት ዜና ወይም ቸነፈር፣ ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና፣ ስራ ለሰሪዉ እሾህ ላጣሪዉ፣ ቃል ኪዳን አፍራሹ፣ የእግዚአብሔር ቸርነት የአርብርኞች ጀግንነት፣ የሰዉ ሆዱ የወፍ ወንዱ የተሰኙ ረጃጅም ተዉኔቶችን ጽፏል። በተለይ ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና የተሰኘዉ ተዉኔት በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ ለ10 ተከታታይ ሳምንታት የታየና ወደ 15 የሚሆኑ ተዋንያን የተሳተፉበት ተዉኔት ነዉ። ከተዘረዘሩት ተዉኔቶች መካከል የሁለቱ ተዉኔቶች ማለትም ስራ ለሰሪዉ እሾህ ላጣሪዉና የእግዚአብሔር ቸርነት ያርበኞች ደግነት በስተቀር ሌሎቹ የተፃፉበት አመተ ምሕረት አይታወቅም። ይህ ጸሀፊ ትዉኔት ከነዚህ ረጃጅም ተዉኔቶች በተጨማሪ በሙዚቃዊ ተዉኔቶችም ይታወቃል። ከደረሳቸዉ ሙዚቃዊ ተዉኔቶች መካከል፦ ጊዜ ወርቅ ነዉ፣ አስራ ሁለት ጠቅላይ ግዛት፣ ብቸኛ የሀሳብ ጓደኛ፣ ጎልማሳዉ መንገደኛ ለፍቅር የማይተኛ፣ የሴት ፍርሀቷ እስከ መቀነቷ፣ ወንድሜ ተነስ ወፎቹ ተንጫጩ፣ አዲስ ፍቅር ያመናቅር የተሰኙ ተዉኔቶችን ደርሷል። ከአጫጭር ተዉኔቶች መካከል ደግሞ፦ ሳይቸግር ጤፍ ብድር፣ የልጃገረድ ጸሎት፣ የሰዉ ግብሩ ክብሩ፣ ዙሮ ዙሮ ሁሉም ዜሮ፣ አዳኞች ከበረሀ ሲመለሱ፣ የቀበሮ ባህታዊ እና ቀዩ ሌሊት ይጠቀሳሉ።

መላኩ በጎሰዉ
ይህ ፀሀፊ ተዉኔት ከፃፋቸዉ ተዉኔቶች መካከል የተገኙት ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም፦ በ1927 ታላቁ ዳኛ እና ነይ ነይ በደመና የተሰኙ ስራዎች ይጠቀሳሉ።

አያልነህ ሙላቱ
እኒህ ደራሲ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ተዉኔቶችን ደርሰዋል። ከነዚህም መካከል፦ እሳት ሲነድ፣ የገጠሯ ፋና፣ የመንታ እናት፣ ዱባና ቅል ጥበበኛዋ ጋለሞታ ደሀ አደግ፣ ሰባራ ዘንግ፣ ድርብ ጭቁን እና ሌሎች ተዉኔቶችን ለህዝብ በመድርክ ያቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ ዐለም፣ ቅሪት፣ ቀዝቃዛዉ ትዳር፣ ጧሪ ልጆች፣ ባልና ሚስት ግርዛት፣ መስከረም ቡሔ፣ የእናት ጡት ያለእድሜ ጋብቻ የተሰኙ ተዉኔቶች ታይተዋል። በኢትዮጵያ ሬድዮ ደግሞ ቤተሰብ፣ ሴት ተማሪ፣ ጠለፋ፣ ዶክተር ሙሉ፣ ሴት ለጓዳ የተሰኙ ተዉኔቶችን አስደምጠዋል።

መላኩ አሻግሬ
መላኩ አሻግሬ ወደ 25 የሚደርሱ ተዉኔቶችን ጽፈዋል። ከነዚህምም መካከል፦ በ1959 ሽፍንፍን፣ በ1962 አየ ሰዉ፣ በ1960 ማሪኝ፣ በ1965 ምን አይነት መሬት ናት፣ በ1954 ዐለም የተሰኙ ተዉኔቶችን ደርሰዋል። ዓመተ ምሕረታቸዉ የማይታወቁት ደግሞ ጊዜና  ገንዘብ፣ ክህደት የኑሮ ስህተት፣ የትም ወርቅ እንዳሻዉ፣ ነፍስ ይማር፣ መጥረጊያ ያለዉ፣ የእሳት ራት፣ ጉድ ፈላ፣ ግንድ አልብስ፣ ህልም ነዉ፣ ይቅርታሽን፣ ማጣትና ማግኘት፣ ባቡሩና ሌሎችም ተዉኔቶች ይጠቀሳሉ። አብዛኞቹ የኮሚዲ ዘዉግ ያዘሉ ናቸዉ።

የድራማ ባህሪያት
ድራማን ከሌሎች የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች (ዘዉጎች) የሚለዩና የራሱ የሆኑትን ግለ ወጥ ባህሪያት እንዲላበሱ የሚያደርጉ ናቸዉ። እነሱም ዉስንና አጠቃላይ ባህሪያት ተብለዉ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ።

የድራማ ዉስን ባህሪያት
ዉስን ባህሪያት የሚባሉት የድራማን መስክ በተናጥል የሚያጠኑትን የመስኩ ምሁራንን፣ ደራሲያንን፣ ሐያሲያንን እዉቀትና ትንታኜ ሳያስፈልጋቸዉ ማንኛዉም ታዳሚ በቀላሉ ሊረዳዉ የሚችለዉ ማለት ነዉ። በዚህ መሰረትም ዉስን ባህሪያት ተብለዉ የሚጠቀሱት፦
  • በጽሑፈ ተዉኔቱ ዉስጥ ተስለዉ የሚገኙ ገጸ ባህሪያትን ሚና ወክለዉ በመድረክ ላይ የሚተዉኑ የገሀዱ ዐለም ሰዎች መኖር፣
  • በመድረክ ላይ በትወና ተግባር የተሰማሩትን ተዋንያን በአዳራሽ ተቀምጠዉ የሚመለከቱ ሰዎች መኖር፣
  • በምልልስና በድርጊት የመድረክ ክዋኔ መኖር፣
  • የተማረዉንም ሆነ ያልተማረዉን ታዳሚ እኩል ማነሳሳት ወይም ማነቃቃት መቻል፣
  • በሰዉ አዕምሮ ዉስጥ አንዳች ነገር ቀርፆ የማስቀረት ሀይሉ የላቀ መሆኑ እና ፈጣን ለዉጥ ማምጣት መቻል፣
  • የብዙ ሙያተኞች ተሳትፎ መኖር

የድራማ አጤቃላይ ባህሪያት
የድራማ አጠቃላይ ባህሪያት ሲባል ስለ ስነ ጽሑፍ ዘርፎች በተለይ ስለ ድራማ በቂ የሆነ የንድፈ ሐሳብ እዉቀት ኖሮት ጥበቡን መተንተን፣ ማጥናት፣ መመዘን የሚችል ሰዉ ስራዉን የሚመዝንባቸዉና በመከላከያነት የሚጠቀምባቸዉ ማለት ነዉ። እነዚህም ባህሪያት፦
  • ቀዉስ፣ ዉዥንብርና ግራ መጋባት መኖር፣
  • የተዘወተረ መሰረታዊ መዋቅር መኖር
  • ትኩረተ ብዙሀንን ማግኘት
  • ግልጽነት፣ ቀጥተኝነት፣ ለመረዳት የማያስቸግር መሆን
  • የተለየ የአተራረክ ብልሀት መኖር
  • የተለየ የታሪክ አነሳስ እና የመረጣ ፋይዳ መኖር
  • ተመድራኪነት